ቢሮው ከተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ለተውጣጡ አካላት በበጀት ዝግጅትና ሂደት ዙሪያ የዜጎች ግንዛቤና ተሳትፎ ለማሳደግ የሚያስችል አቅም ግንባታ ስልጠና ለጂኔላ፣አሚር ኑር፣ ሸንኮርና አቦከር ወረዳ መስተዳደር ለተውጣጡ የማህበረሰብ ክፍሎች ሰጥቷል። የስልጠናው አላማ በመንግስት በጀት ሂደት ላይ የዜጎችን ግንዛቤ፣ ተሳትፎና የመረጃ ተደራሽነትን በማሳደግ ፍትሃዊ የሆነ ማህበረሰባዊ አገልግሎቶች ማዳረስና ለውጥ ማምጣት እንደሆነ ተገልጿል። ዜጎቹን ስለ ወረዳው በጀት አጠቃቀምና አፈጻፀም የማሳወቅና በውይይት ወቅት የሚኖሩ ሃሳቦችን በማካተት የቀጣይ በጀት ዓመት ዕቅድን ከወረዳው ዜጎች ፍላጎት አንፃር የተሟላ ማድረግ ዋነኛው እንደሆነ ተጠቁሟል፡፡ በዚህም ሂደት ውስጥ ዜጎች በየወረዳቸው በሚኖሩ እንቅስቃሴዎች ባለቤት እንዲሆኑ በማድረግ በቀጣይም የጠያቂነት አቅማቸውን ማዳበር እንዲሁም የመንግስት ተቋማት የግልፅነት አሠራርን እንዲከተሉ ለማድረግ የስልጠና መድረኩ በእጅጉ እንደሚረዳ ተገልጿል፡፡