መስከረም 16/2019 | ሐረር/ የሐረሪ ሕዝብ ክልላዊ መንግሥት የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ቢሮ የ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸምን እና የ2019 በጀት ዓመት ዕቅድን በተመለከተ ከቢሮው ሠራተኞች ጋር የውይይት መድረክ አካሂዷል።
በመድረኩ የ2018 በጀት ዓመት አፈጻጸም በዝርዝር የተገመገመ ሲሆን፣ በ2019 በጀት ዓመት ሊተኮርባቸው የሚገቡ የሥራ አቅጣጫዎችም ተቀምጠዋል። በዕለቱም በ2018 በጀት ዓመት የላቀ የሥራ አፈጻጸም ላስመዘገቡ ዳይሬክተሮችና ሠራተኞች የእውቅና ሽልማት ተበርክቷል።
የመድረኩን መክፈቻ ንግግር ያደረጉት የቢሮው ኃላፊ አቶ መሀመድ ያህያ ቢሮው በ2018 የሥራ ዓመት አበረታች አፈጻጸም ማስመዝገቡን ገልጸው የተገኘው ውጤት የአመራሩና የመላው ሠራተኛ የጋራ ጥረት ውጤት መሆኑን ጠቁመዋል። ያለፈውን የሥራ ዓመት በመገምገም፣ የተከናወኑና ያልተከናወኑ ሥራዎችን በመለየት ጠንካራ ጎኖችን ማጠናከር እና ከአፈጻጸም ወቅት ከተስተዋሉ ስህተቶችና ክፍተቶች በመማር ወደ 2019 በጀት ዓመት በተሻለ የሥራ ባህል፣ በተሻለ አቅምና በተሻለ ውጤት መሻገር እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ቢሮ ኃላፊው አክለውም የቢሮው ሥራ በቁጥር ወይም በተከናወኑ ተግባራት ብቻ የሚለካ እንዳልሆነ ገልጸው፣ ሥራው ከክልሉ ሀብትና ከበጀት ውሳኔዎች ጋር የተያያዘ ከመሆኑም በላይ የመንግሥትን የፋይናንስ ግልጽነትና ተጠያቂነት፣ የልማት ፕሮጀክቶችን እንዲሁም የሕዝብን ሀብትና ጥቅም የሚመለከት ከፍተኛ ኃላፊነት መሆኑን አፅንኦት ሰጥተዋል። የቢሮው ራዕይም ዘመናዊ የፋይናንስ አስተዳደር ሥርዓት በመዘርጋት ለክልሉ የኢኮኖሚ ዕድገት የራሱን ድርሻ በብቃትና በጥራት መወጣት መሆኑን አስገንዝበዋል።
አቶ መሀመድ የ2019 በጀት ዓመት የቢሮውን የሥራ አቅጣጫዎች በማብራራት፣ የፕሮግራም በጀት አሠራርን ማጠናከር፣ የሀብት አጠቃቀምን ከውጤት ጋር ማስተሳሰር፣ የዲጂታል አሠራርን በግዥና በንብረት አስተዳደር ማስፋት፣ የፋይናንስ ግልጽነትንና ተጠያቂነትን ማጠናከር፣ የቢሮውን የአገልግሎት አሰጣጥና አስተዳደር ሪፎርም ማካሄድ እንዲሁም በሁሉም የቢሮው ሥራዎች ውስጥ ውጤታማነትንና መልካም የሥራ ባህልን ማስረጽ ዋና ትኩረት የሚሰጣቸው ጉዳዮች መሆናቸውን ገልጸዋል።
የቢሮው ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ያህያ አብዱራሂም በበኩላቸው በ2018 በጀት ዓመት ጠንካራ አሠራሮች በመዘርጋታቸው አበረታች ውጤቶች መመዝገባቸውን ገልጸው፣ በዕቅድ አፈጻጸም ወቅት የታዩ መልካም ልምዶችን ማስቀጠል፣ የመንግሥት አገልግሎትና አስተዳደር ሪፎርምን ማጠናከር እና የተጀመሩ የዲጂታላይዜሽን ሥራዎችን ማስፋት እንደሚገባ አሳስበዋል። ይህም ቀልጣፋ፣ ውጤታማና የተቀናጀ አሠራር ለማስፈን የሚያግዝ መሆኑን ገልጸዋል።
በመድረኩ የቢሮው የ2018 በጀት ዓመት የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት በዕቅድ ክትትልና ግምገማ ዳይሬክተር ወ/ሮ ሲትራ አብዱራህማን ቀርቧል። በሪፖርቱም የ2018 በጀት ዓመት የቢሮው ሥራዎች በአራት ዋና ዋና ስትራቴጂካዊ ግቦች ላይ ተመስርተው መከናወናቸው ተገልጿል። ሪፖርቱ የተከናወኑ ሥራዎችንና የተገኙ ውጤቶችን ከማቅረብ ባለፈ፣ በአፈጻጸም ወቅት የታዩ ችግሮችን፣ በ2019 በጀት ዓመት ሊሻሻሉ የሚገባቸውን ጉዳዮችና ቀጣይ ስትራቴጂካዊ ዕቅዶችንም አካቷል።
በሪፖርቱ ላይ የቢሮው ሠራተኞች የተለያዩ ሀሳቦችንና ጥያቄዎችን ያነሱ ሲሆን፣ ለተነሱት ጥያቄዎችና ሀሳቦች በዳይሬክተሮችና በቢሮው ኃላፊዎች ማብራሪያና ምላሽ ተሰጥቷል። ውይይቱ የ2018 በጀት ዓመት ልምዶችንና አፈጻጸሞችን በመገምገም በ2019 በጀት ዓመት የሚፈጸሙ ሥራዎችን በተሻለ ቅንጅት፣ በውጤት ተኮር አፈጻጸምና በተጠያቂነት ለማከናወን የጋራ ግንዛቤ ለመፍጠር አስችሏል።
በመጨረሻም በ2018 በጀት ዓመት የላቀ የሥራ አፈጻጸም ላስመዘገቡ ዳይሬክተሮችና ሠራተኞች የእውቅና ሽልማት ተበርክቷል። በዚህ ወቅት አቶ መሀመድ ያህያ እውቅና የሚሰጠው አንድ ሰው “አንተ ብቻ ትችላለህ” ወይም “አንቺ ብቻ ትችያለሽ” ለማለት ሳይሆን፣ “ጥሩ ሥራ ይታያል፣ ይመዘናል፣ ይከበራል፣ ለሌሎችም ምሳሌ ይሆናል” የሚል የሥራ ባህል ለመገንባት መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም መሠረት ቢሮው የ2019 በጀት ዓመትን በተሻለ የሥራ ባህል፣ በተጠናከረ አሠራር፣ በዲጂታል ለውጥ፣ በግልጽነትና ተጠያቂነት እንዲሁም በውጤት ተኮር አፈጻጸም ለመምራት የሚያስችሉ የሥራ አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ የውይይት መድረኩን አጠናቋል።












