የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ቢሮ እና ፕላንና ልማት ኮሚሽን በባለፉት 6 ወራት የክልሉ የካፒታል ፕሮጀክቶች ያሉበትን ደረጃ ለማወቅና እያጋጠሙ ያሉ ችግሮች ለይቶ መፍትሔ ለመስጠት ያለመ ውይይት ከርዕሰ መስተዳድሩ አማካሪዎች ጋር አካሄዱ።
በውይይታቸውም የፕሮጀክቶቹን የ6 ወራት የፋይናንሺያልና የፊዚካል አፈፃፀም ላይ መክረዋል።
በ2016 በጀት አመት በግማሽ አመቱ ብር 888,2 ሚሊዮን የካፒታከል ወጪ ታቅዶ ብር 722,9 ሚሊዮን ወይም የእቅዱን 81% አፈፃፀም በጀት ስራ ላይ የዋለ መሆኑ ተገልጿል።
ነባርና አዳዲስ ፕሮጀክቶችን ጨምሮ በክልሉ ብዙ ወጪ ወጥቶባቸው እየተሠሩ ያሉ በርካታ የካፒታል ፕሮጀክቶች እንዳሉና ነገር ግን የእነዚህ ፕሮጀክቶች አፈጻጸም በሚፈለገው ደረጃ እንዳልሆነም ተገልጿል።
በተያዘላቸው ጊዜ መርሃ ግብር መሰረትም ባለመጠናቀቃቸው አንዳንድ ፕሮጀክቶችን የፊዚካል እና የፋይናንሺያል አፈጻጸማቸው ተጣጥሞ እንዳልሄደም ሃሳብ ተነስቷል፡፡
ጠንካራ ተጠያቂነትን በማስፈን የፕሮጀክቶችን አፈጻጸም ውጤታማ ለማድረግ የክትትልና ግምገማ እንደሚያስፈልግና የፕሮጀክት ባለቤት ተቋማት እና የሚመለከታቸው አካላት ለጉዳዩ ትኩረት ሊሰጡት እንደሚገባም የርዕሰ መስተዳደሩ አማካሪዎች ተናግረዋል፡፡
ዝቅተኛ አፈፃፀም ለታየባቸው የካፒታል ፕሮጀክቶች የፊዝካልና የወጪን አቀናጅቶ በዕቅድ አለመስራት እንዲሁም አስፈላጊ የሆነ ክትትልና ቁጥጥር አለማድረግ በምክንያትነት ተጠቅሷል።
የፕሮጀክት የአመራር ስራው የጥራት፣ ጊዜና ሀብትን በአግባቡ መጠቀም ላይ ክፍተቶች እንዳሉበት በጥራት፣ በተመደበላቸው ጊዜ እና ሀብት በማጠናቀቅ በኩል አሁንም ፈተና ሆኖ መቀጠሉን የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሃላፊ አቶ መሐመድ ያህያ ጠቁመዋል።
ፕሮጅክቶቹ በጊዜ አለመጠናቀቃቸው ለተፈለገው ዓላማ ካለመድረሳቸው ባሻገር ተጨማሪ ሀብት፣ ጉልበት እና ጊዜ እንዲባክን ያደርጋሉ ብለዋል፡፡
በ2016 በጀት ዓመት የተሻለ የፕሮጀክት አፈጻጸም አመራር ሥርዓት በመከተልና በዘርፉ ያሉ ችግሮችን በመቅረፍ የክልሉ መንግሥት የልማት ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ፣ በጀት እና በጥራት እንዲጠናቀቁ በትኩረት መስራት ያስፈልጋል ሲሉ ተናግረዋል፡፡








